አቤቱታ አቀራረብ ሥነ- ሥርዓት

1. ቅሬታ ወይም አቤቱታ ያለው ተገልጋይ

አቤቱታውን ወይም ቅሬታውን በራሱ ወይም በህጋዊ ወኪሉ አማካኝነት በቃል ወይም በፅሁፍ፣ በኢሜል ወይም ማንኛዉንም ቴክኖሎጂ ተጠቅሞ ሊያቀርብ ይችላል፤ አቀራረቡም ግልፅ፣ ቀላል ሆኖ የግድ የባለሙያ ድጋፍን የሚጠይቅ መሆን አይኖርበትም፤

2. ዘርፉ የተገልጋዩን ቅሬታ ወይም አቤቱታ ሲቀበል የሚከተሉትን ነጥቦች ማጣራት ይኖርበታል፡-

  1. የቀረበዉ አቤቱታ ወይም ቅሬታ ዘርፉ የማየት ስልጣን ያለዉ ስለመሆኑ፣
  2. የቀረበዉ ቅሬታ ወይም አቤቱታ በማቅረቢያ ቅፅ መሰረት በተገቢዉ ተሞልቶ መቅረቡን፣
  3. የቅሬታው ወይም የአቤቱታው ጭብጥ ፣ ጉዳዩ የቀረበበት ዕለት፣ ቀንና ወር ተጠቅሶ መመዝገቡንና ለባለጉዳዩ ማረጋገጫ መሰጠቱን፣
  4. በየደረጃው የተሰጡት የመጨረሻ ምላሾች ወይም ዉሳኔዎች መያያዛቸውን እና ካልተያያዘም አቤት ባዩ ያቀረባቸዉ ተገቢነት ያላቸዉ መረጃዎች ምን እንደሆኑ፣
  5. ሌሎች ከጉዳዩ ጋር አግባብነት ያላቸው መረጃዎች ካሉ በቅጹ ላይ በትክክል መሞላታቸውን፣
  6. በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (1) በተጠቀሰዉ መሰረት አቤት ባይ ወይም ህጋዊ ወኪሉ ያቀረባቸዉ መረጃዎች ትክክለኛ ስለመሆናቸዉ በአቅራቢዉ ፊርማ የተረጋገጠ መሆኑን፤

3. በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (2) ከተራ ፊደል "1" እስከ "5" የተጠቀሱ ሁኔታዎች ከተጣሩ በኋላ ለባለጉዳዩ መልስ የሚሰጥበት ጊዜ መገለፅ አለበት፤

4. ቅሬታውን ወይም አቤቱታውን የማጣራት ሥርዓት እንደሚከተለዉ ይሆናል፡-

  1. በዚህ ደንብ የተጠቀሱት ጉዳዮች ተደራጅተው መቅረባቸዉ ከተረጋገጠ በኋላ ዘርፉ የቀረበለትን ጉዳይ ከደጋፊ ሰነዶችን ጋር በማገናዘብ በዝርዝር ይመረምራል፣
  2. አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ዘርፉ ከባለጉዳይ ጋር ይወያያል፣ ግልፅ ባልሆኑ ጉዳዮች ዙሪያ ተጨማሪ ማብራሪያ ይጠይቃል፣
  3. አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ቅሬታው ወይም አቤቱታው በተፈጠረበት ወይም ክርክር ያስነሰው ንብረት ያለበት አካባቢ ወይም መስሪያ ቤት በአካል ተገኝቶ ይመለከታል፣ የቴክኒክና ሌሎች የማጣራት ሥራዎችን ይሰራል፣
  4. አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ በየደረጃ ውሳኔ የሰጡ ወይም በተቋሙ ስልጣንና ኃላፊነት መሰረት በጉዳዩ ዙሪያ ቀደም ብሎ አስተያየት የሰጡ ተቋማት ወይም የሚመለከተዉ ኃላፊ ተጨማሪ ማብራሪያ ወይም አስተያየት እንዲሰጡ ወይም በአካል ተገኝተዉ ማብራሪያ እንዲስጡ ያደርጋል፣
  5. ለትክክለኛ ፍትህ አሰጣጥ ሲባል ዘርፉ እንደአስፈላጊነቱ የቀረበዉን ጉዳዩ ያውቃሉ ብሎ ያመነባቸዉን ግለሰቦች ወይም ግለሰብ ወይም የህብረተሰብ ክፍሎችን ወይም ተቋማትን ጠርቶ ያነጋግራል፤ የቃልም ሆነ የጹሁፍ ማብራሪያ ይቀበላል፣
  6. ለቀረበዉ ጉዳይ ዝርዝር የማጣራት ሥራ ከሰራ ቦኋላ በሥራ ላይ ካሉ ህጎች ጋር በማገናዘብ በመጨረሻም ውሳኔ ይሰጣል፣
  7. የተወሰነው ውሳኔ በዘርፉ በሚመለከተዉ ፈፃሚ ወይም የሥራ ክፍል ኃላፊ ተፈርሞና የመንግሥት መሥሪያ ቤቱ ማህተም ተደርጎበት ወጭ ይሆናል፣
  8. የውሳኔዉን ቅጅ በሸኚ ደብዳቤ ለባለጉዳዩና ለሚመለከተዉ አካል እንዲፈፀም ወይም እንዲያውቅ በአድራሻ በሸኚ ደብዳቤ ይልካል፤ አፈፃፀሙን ይከታተላል፡፡